የባንኩ የባለአክሲዮኖች 12ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ሕዳር 27 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ
ሚሊኒየም አዳራሽ በተሳካ ሁኔታ አካሂዷል::
አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ አ.ማ በተጠናቀቀው የሂሳብ ዓመት 1.7 ቢሊዮን ብር ገቢ
ማስመዝገቡን ገለፀ

በጉዔው ላይ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ካሳሁን በቀለ እ.ኤ.አ. ሰኔ 30 ቀን 2023 ዓ.ም. የተጠናቀቀውን የ12ኛ የሂሳብ ዓመት የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት ለመደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ አቅርበዋል፡፡
በቀረበው ሪፖርት መሰረት ባንኩ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ቢያልፍም በሂሳብ ዓመቱ የነበረው አፈፃፀም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር አበረታች የሚባል ነበር ሲሉ ገልፀዋል፡፡ በዚህም እስከ እ.ኤ.አ
ሰኔ 30 ቀን 2023 የባንኩ አጠቃላይ ሐብት ብር 12.6 ቢሊዮን እና አጠቃላይ ካፒታል ብር 2.6 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በብር 1.8 ቢሊዮን (17 በመቶ) እና
በብር 408.9 ሚሊዮን (19 በመቶ) በተከታታይ ዕድገት አስመዝግቧል።

ባንኩ ለደምበኞች የሰጠው አጠቃላይ የብድር መጠን ብር 7.6 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ24 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ባንኩ ለደንበኞች የተሰጠ ብድር ጤናማነት
ለማረጋገጥ ጥንቃቄ የተሞላበት የብድር አስተዳደር ስርዓት ዘርግቶ ተግባራዊ በማድረጉ አጠራጣሪ ብድሮች ከጠቅላላ ብድር ያላቸው ድርሻ 2.5 በመቶ የደረሰ ሲሆን ይህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
ካስቀመጠው የ5 በመቶ ጣሪያ አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ተቀማጭ ገንዘብ በተመለከተ በሂሳብ ዓመቱ የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ በ17 በመቶ በማደግ ብር 9.2 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ደግሞ 146.7 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ባንኩ በሂሳብ ዓመቱ
ከተለያዩ ገቢዎች ብር 1.7 ቢሊዮን ገቢ አግኝቷል፡፡ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ10 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በዚህም ከታክስ በፊት እና በኋላ ብር 306.8 ሚሊዮን እና ብር 223.5 ሚሊዮን
ትርፍ በተከታታይ አስመዝግቧል፡፡ የደምበኞች ብዛት በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረ ሲሆን እ.ኤ.አ. እስከ ሰኔ 30 ቀን 2023 ድረስ 495,775 ደርሷል ብለዋል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ35
በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ በተያያዘም ባንኩ የቅርንጫፍ ስርጭቱን 132 አድርሷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ከባለአክሲዮኖች ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የዋና መስሪያ ቤት ግንባታን በተመለከተ አዲስ አበባ ንግድ ስራ ኮሌጅ ፊት ለፊት የተወሰነልንን
ቦታ ከአዲስ አበባ መስተዳድር ቦታ ለመረከብ ጥረት ቢደረግም በኪራይ ቤቶች አስተዳደር በኩል ተለዋጭ ቦታ የተሰጣቸው ቢሆንም ቦታውን ራሳችን እናለማለን በሚል እስካሁን የቦታ ርክክብ አልተደረገም፡፡
ቦታው የፋይናንስ ተቋማት ማዕከል በመሆኑ እና ከመስተዳድሩም ለባንኩ እንደሚገባ ስለታመነበት ባንኩ በዚህ ዓመት ለመረከብ አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት አድርጎ ቦታውን እንደሚረከብ ገልፀዋል::

በሌላ በኩል የባንኩን የትርፍ ድርሻ መቀነስ አስመልክተው ባንኩ በበጅት ዓመቱ ከፍተኛ የወጪ ምንዛሬ ግኝት ቢያስመዘገብም በብሔራዊ ባንክ 70 በመቶ የሚሆነውን ግኝት ለመሸጥ በመገደዱ ከፍተኛ የሆነ
ገቢ ማጣቱን ገልፀዋል፡፡ በዚህም ምክያት ለባለአክሲዮኑ የሚከፍለው የትርፍ ድርሻ ከባለፈው ዓመት አንፃር መቀነሱን ለባለአክሲዮኖች አስገንዝበዋል፡፡

ከዲጂታላይዜሽን ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጥያቄዎች የቦርድ ሰብሳቢው ባንኩ ዘመናዊ የሆነ የኮር ባንኪንግ፣ የሞባይል እንዲሁም የኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን በተለይ የሞባይል ባንኪንግ
አገልግሎቱ ዓለም ላይ ስመጥር ከሚባሉ አቅራቢዎች የተገዛና በአገልግሎቱም እጅግ ዘመናዊ እና ብዙ የራሱ መለያዎች እንዳሉት እና በደንበኞች የተወደደ መሆኑን ገልጸው ባለአክሲዮኖች እንዲጠቀሙት ጥሪ
አቅርበዋል፡፡

ባንኩ በቀጣይ የዋና መስሪያ ቤት ግንባታ ፤ ተጨማሪ አክሲዮን መሸጥ ፤ የመዋቅር ማሻሻያ ተግባራዊ ማድረግ እና የባንኩን መለያ አርማ በማሻሻል በይበልጥ በደንበኞቹ ተመራጪ ለመሆን እንደሚሰራ
ገልፀዋል፡፡